Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የኢፌዲሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተርለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት መንግስት ሶስት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደስራ መግባቱን አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ግሽበት ሶስት ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ እነሱም የዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት እንዲሁም በሀገር ውስጥ መሰረታዊ ፍላጎቶች ጋር የሚመጣጠን ምርት አለመኖሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት መንግሥት ባስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት  የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቀድ በማውጣት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም እና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ሶስት መፍትሄዎችን አስቀምጦ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫዎቹም በጊዚያዊነት ችግሩን የሚፈቱ እርምጃዎች መውሰድ፣ የመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር እና ህብረተሰቡን የመፍትሄ አካል ማድረግ መሆናቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በዚህም መሰረት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈጽሙ እና የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል ብለዋል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል ግዥ የተፈፀመባቸው ምርቶች በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት በመስኖና በበልግ የተጀመረውን የስንዴ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ በቀጣይ የመኸር ስንዴ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ለማምረት አስፈላጊውን ግብዓት ማቅረብ ላይ ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ የአመራረት እና አመጋገብ ዘይቤውን መቀየር እንዳለበት ጠቁመው÷ ሸቀጦች ወይም ምርት በህገ ወጥ መንገድ እዳይዘዋወሩ በሚያደርገው ቁጥጥር ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መንግሥት በብዙ ቢሊየን ብር ድጎማ የሚገዛቸው መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ሀብቱን እንዲጠብቅና እና ክትትል እንዲያደርግ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአገሪቱ የተፈጠረው የዋጋ ንረት በዋነኛነት በዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ መናር ምክንያት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ለገሰ÷ በመንግሥት ውስጥ ያሉ ሌቦችና ስግብግብ ነጋዴዎች የችግሩ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የመሠረታዊ ሸቀጣሸቀጦችን ፍሰትና የገበያ ስርዓት ለማሻሻል በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ አስቀምጦ እና ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቋቋም የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ህብረተሰቡም የሚያደርገውን ክትትል እና ቁጥጥር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን የፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያ ለማድረግና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም መንግሥት አስጠንቅቋል፡፡
ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚደረግ ሙከራ መኖሩንም የገለጹት ሚኒስትሩ÷ በተለይም የአማራ እና የኦሮሞን ሕዝብ ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል፡፡
ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር በተያያዘም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራ በአለም አቀፉ የተራድኦ ድርጅቶች አማካይነት በአየርና በየብስ እርዳታ ተደራሽ እየተደረገ መሆንን ገልጸዋል፡፡
በየብስ በተካሄደ የእርዳታ ማጓጓዝ ሥራ ትናንት እርዳታ የጫኑ 13 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቀሌ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ቀሪ ሰባት ተሽከርካሪዎችም በጉዞ ላይ መሆናቸው ጠቁመዋል፡፡
ከሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ እርዳታ እየደረሰ እንዳልሆነ የሚገልጹ አካላት ከሚያሰራጩት የሀሰት መረጃ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version