Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓመት እንኳን አደረሰን – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዕለት እንኳን አደረሰን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ለመላው ኢትዮጵያውያን!
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዕለት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ እንኳን አብሮ አደረሰን።
እነሆ! . . . ለሺህ ዓመታት ሲፈስ የነበረው የዓባይ ወንዝ ለሃገራችን ሁነኛ የልማት አቅም ለመሆን በሩ የተከፈተበትን ታሪካዊ ዕለት በጋራ ለመዘከር አበቃን!
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ግድቡ ወሳኝ የግንባታ ሂደቶችን በማለፍ በአሁን ጊዜ የቅድመ~ሃይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በዚህ ታሪካዊ የግንባታ ጉዞ የህዝባችን ሁለገብ ድጋፍ፤ የመንግስት ጠንካራ አመራር፤ የዲያስፖራ ወገኖቻችን እገዛ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ርብርብ በእጅጉ የሚደነቅ እና የሚያኮራ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ለደማቅ አበርክቷችሁ በመንግስታችን እና በመላው የሃገራችን ህዝብ ስም ከፍ ያለ ምስጋና እና አክብሮቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።
በቀጣይ ቀሪ የግንባታ ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም የሰፊውን ማህበረሰብ ተሳትፎ እና ድጋፍ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በተለያየ መልክ የሚገለፁ ችግሮች ሃገራችንን እየፈተኗት ቢሆንም፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ የተስተዋለውን የፀና ህዝባዊ አንድነት እና ህብረት የበለጠ አጠናክሮ በድል ማሻገር ይጠይቃል።
በመጨረሻም ከቀደሙ አባቶቻችን የወረስነውን የድል አድራጊነት ጠንካራ መንፈስ ለመጪው ትውልድ የታፈረች፣ የተከበረች እና የበለፀገች ሃገር ለማስረከብ አንድነታችንን እና ህብረታችንን አጥብቀን እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
“ግድባችን የአንድነታችን ብርሃን ነው!”
አመሰግናለሁ!
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version