የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍን ለማድረስ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው – የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ

By Alemayehu Geremew

April 01, 2022

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ዶክተር አኔቴ ዌበር በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍን ለማድረስ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት አደነቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከልዩ ልዑኩ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በትግራይ ክልል ባለው የሰብአዊ ድጋፍ እንዲሁም በጂኦፖለቲካዊ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፥ በቅርቡ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተደረሰው ተኩስ አቁም በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

አያይዘውም በመንግስት ከተደረሰው ተኩስ አቁም ባሻገር ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ 22 የዓለም ምግብ ፕፎግራም ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል።