Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍን ለማድረስ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው – የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ዶክተር አኔቴ ዌበር በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍን ለማድረስ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት አደነቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከልዩ ልዑኩ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በትግራይ ክልል ባለው የሰብአዊ ድጋፍ እንዲሁም በጂኦፖለቲካዊ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፥ በቅርቡ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተደረሰው ተኩስ አቁም በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

አያይዘውም በመንግስት ከተደረሰው ተኩስ አቁም ባሻገር ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ 22 የዓለም ምግብ ፕፎግራም ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል።

ህወሓት ሰበብ እየደረደረ መቀጠሉ እንዳሳሰባቸው የገለጹት አቶ ደመቀ መኮንን፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የህወሓት ታጣቂዎች ለተኩስ አቁሙ ተገዢ እንዲሆኑ ጫና ሊያሳድርባቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አቶ ደመቀ በውይይታቸው ወቅት በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በመንግስት እየተወሰዱ ስላሉ አወንታዊ እርምጃዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ታዋቂ ፖለቲከኞች ከእስር መፈታታቸውን፣ በሃገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀደም ብሎ መነሳቱን እንዲሁም በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የተዘጋጀውን ብሄራዊ ምክክር ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
Exit mobile version