Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሐረሪ ክልል በግማሽ ዓመቱ ከ580 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪን ክልል ገቢ ለማሻሻል በተከናወኑ አዳዲስ የአሰራር ሥርዓቶች በግማሽ ዓመቱ ከ580 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልጹ፡፡
እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ የመስተዳድሩ የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ ለ6 ሺህ 173 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ4 ሺህ 988 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን እና ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱ ተጠቁሟል፡፡
የቱሪዝም ምርቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ በተከናወነ ተግባርም በግማሽ አመቱ 60 ሺህ የሀገር ውስጥ እንዲሁም 447 የውጭ ዜጎች ክልሉን መጎብኘታቸውን የጠቆመት ርዕሰ መስተዳድሩ አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ከመከላከልና ከመቀነስ ጋር ተያይዞም በክልሉ ባለፉት 6 ወራት ከ508 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እና ሌሎች መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ መሰራጨቱን እንዲሁም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ በሚያደርጉ አካላት ላይ ቁጥጥር የማድረግና የአቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ 224 ሺህ 375 ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ቢሆንም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፀፃፀር የ23 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና ለዚህም በምርት ዘመኑ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በክልሉ ገጠርን ከከተማ የሚያገናኙ 45 ኪሎሜትር የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው ሆኖም ግን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በአግባቡ ባለመከናወናቸው፥ ሥራዎችን በወቅቱ አለመጀመር እንዲሁም በዋጋ ንረት ተፅዕኖ ምክንያት የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በሚፈለገው መልኩ እንዳይሆን አድርጓል ብለዋል፡፡
ህገወጥ የመሬት ወረራንና ህገወጥ ግንባታን ለመከላከል የክልሉ ሰላም ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
በማኅበራዊ ዘርፍ በተለይም በትምህርትና ጤና ዘርፎች ተደራሽነትንና ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውም ተመልክቷል፡፡
ህገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል፣ የክልሉን ሠላም ለማረጋገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እና የህዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ ተግባራት ለማከናወን እንደሚሰራ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version