Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለ2014/15 የምርት ዘመን የሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ማድረስ እንደሚቻል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2014/15 የምርት ዘመን የሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ማድረስ እንደሚቻል የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ መንግስት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በወቅቱ ለማከናወን ብዙ ፈተናዎችን ያስተናገደ መሆኑን አንስተው አሁን ግን ከ12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ግዥ መፈፀሙን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሚሆነው ጅቡቲ ወደብ ላይ ደርሶ 3 ሚሊየን ኩንታሉ ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ችሏል ነው ያሉት።

 

ለአርሶ አደሩ በወቅቱ መሰራጨት እና መድረስ እንዲችልም ከባድ ተሽከርካሪዎችን እና የባቡር ፉርጎን በመጠቀም በቀን በአማካይ ከ70  እስከ 80  ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ በቀን ወደ ሃገር ውስጥ እየገባ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ይህም በመሆኑ  የአርሶ አደሩ  የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ላይ እጥረት እንደማይፈጠር ሃላፊው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ዓለም አቀፍ ገበያ ከዚህ በፊት ይገዛበት ከነበረው ከእጥፍ በላይ መሆኑ ያነሱት ሃላፊው ይህን ተከትሎ በሀገር ውስጥ ያለው ዋጋ ከፍ ሊል ችሏል ብለዋል።
ሆኖም የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይኖር በግብርና ሚኒስቴር ጥናት መሰረት መገዛቱንም ሃላፊው አቶ ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል።
በይስማው አደራው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version