አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የመንግስት ጉባኤ እየተሳተፉ ነው፡፡
በየአመቱ በሚካሄደው የዱባይ ዓለም አቀፍ የመንግስት ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሚኒስትሩ ጎንለጎንም የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል።
በዚህም ከደቡብ አፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ቦንጊኮሲ ኢማኑኤል እና ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የአርቲፊሻል ኢንቴሌጀንስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚና ሪሞት ወርክ አፕሊኬሽን ሚኒስትር ኦማር ቢን ሱልጣን አል ኦላማ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡብ አፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር መስከረም 2014 ዓ.ም. በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ መክረዋል።
በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት የማስፈፀሚያ ዕቅዱ በኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ዘርፍ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በባዮቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር፣ በስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በስታርት አፕ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የአርቲፊሻል ኢንተሌጀንስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚና ሪሞት ወርክ አፕሊኬሽን ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በአርቲፊሻል ኢንተሌጀንስ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ በሁለቱ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች መካከል ስለሚደረግ ቀጣይ ትብብር ተወያይተው በቀጣይ ስለሚሰሩ ተግባራት ላይ ከመግባባት ደርሰዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!