Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በምስራቅ ሸዋ ዞን ለኦፕሬሽን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት በርካታ አባላት መሞታቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለፀ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሸዋ ዞን ቆርኬ/አውራ ጎዳና ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ለኦፕሬሽን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የክልሉ ሚሊሻ አባላት ላይ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት በርካታ የፀጥታ አባላት መሞታቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለፀ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬርት እንደገለፁት፥ መጋቢት 20 ቀን 2014 ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባለው ልዩ ሥፍራ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች በጉዞ ላይ በነበሩት የህዝብ ሚሊሻና የፖሊስ አባላት ላይ ባደረሱት ዘግናኝ ጥቃት ነው የፀጥታ አባላቱ የሞቱት።

ጽንፈኛ ኃይሎቹ ግድያውን ከፈፀሙ በኋላ አስክሬን እንዳይነሳ ከልክለው መቆየታቸውንና በቦታው የፌደራል የፀጥታ ሀይል ከገባ በኋላ በመጨረሻም ማንሳት እንደተቻለ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ።

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳም በተከሰተው የጽጥታ ችግር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሡን ዛሬ ማስታወቁ ይታወቃል።

Exit mobile version