Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ8ኛው የበርሊን የኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ8ኛው የበርሊን የኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ነው፡፡
በጉባኤው የ50 አገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች በአካል ተገኝተው ሌሎቹ ደግሞ በበይነ መረብ በቀጥታ እየተሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ10 አገራት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሮች እየተሳተፉ ሲሆን÷ ጉባኤው ዘንድሮ ̎ከምኞት ወደ ተግባር“ በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
ጉባኤው በተለይ ታዳጊ አገራት ለዜጎቻቸው ኢነርጂ ለማቅረብ ያላቸውን ህልም ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እና ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚመከርበት እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የህዝብ ቁጥር መሰረት ከፍተኛ የሃይል ፍላጎት በመኖሩ ይህም በኢነርጂ ልማት ለሚሰማሩ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ሰፊ የገበያ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢነርጂ ሴክተር ሪፎርም ፣ ታዳሽ ወይንም ከብክለት የጸዳ ሃይልን ለማጎልበት ያላት ቁርጠኝነት፣ ምስራቅ አፈሪካን በሃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ያለውን ስራ መሰረት በማድረግ በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተሞክሮዋን እንድታቀርብ ተጋብዛለች፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋም የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡
ከጉባኤው በተጓዳኝ ከተለያዩ አገራት አቻ ሚኒስትሮች ጋር የኢትዮጵያን ብሎም ዓለም አቀፉን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ፍሬያማ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version