Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሳለጥ የተለያዩ ስራዎች ማከናወኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚላከውን አቅርቦት ለማሳለጥ ሲል ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ የተለያዩ ስራዎች ማከናወኑን ገለፀ።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥቷል።

መንግስት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፥ ሰብዓዊነትን መሰረት በማድረግ ግጭት ማቆሙን ካወጀ በኋላ ሳምንቱን ሙሉ ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ በአየር እንዲያጓጓዙ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች መፍቀዱን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት መድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁሶች፣ ገንዘብ እና አልሚ ምግቦች በተቻለ መጠን በአየር መጓጓዝ መጀመራቸውን ጠቅሷል።

ለሌሎችም ዓለምአቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሰብአዊ እርዳታን በአየር እንዲያጓጉዙ ፈቃድ መስጠቱን የገለፀው መንግስት፥ የተቋማቱ የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በጉዳዩ ላይ ፈጣን እርምጃ ወስዷል ነው ያለው።

የረድኤት አቅርቦቱን ለማስፋት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በ43 የጭነት ተሽከርካሪዎች አማካኝነት በአፋር ክልል በአብአላ በኩል በየብስ የምግብ እህል እርዳታ እንዲያጓጉዝ ፈቃድ መስጠቱንም ገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥ 20 ተሽከርካሪዎች በሰመራ ቆመው እንደሚገኙ አስታውቋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ያሉትን አማራጮች ሁሉ እየተጠቀመ መሆኑን ገልጾ፥ ነገር ግን በሌላ በኩል ያለው አካል እስካሁን ተባባሪ አለመሆኑንና የዕርዳታ አቅርቦቱን ሂደት እያሰናከለ መሆኑን ነው ያመለከተው።

እነዚህ ፈቃድ ያገኙ 43 የምግብ እርዳታ የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል መግባት ያልቻሉትም የህወሃት ታጣቂዎች አብአላ ላይ መንገድ በመዝጋታቸው መሆኑን መንግስት በመግለጫው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የረድኤት አቅርቦቱን ለማሳለጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ኣካለት ጋር በቅርበት ለመስራት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጠው መግለጫው፥ የህወሃት ታጣቂዎች የተሳሳተ መረጃ ከመንዛት ይልቅ ለህዝቡ እርዳታ የሚቀርብበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው ነው ያሳሰበው።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የትግራይ ታጣቂዎች በሃይል ከያዙበት እና ሰላማዊ ሰውን መያዣ ካደረጉባቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ወረዳዎች ለቀው እንዲወጡ እና ለተኩስ አቁም ውሳኔው ተገዢ እንዲሆኑ ግፊት እንዲያደርግ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የእርዳታ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን በጋራ እንደሚሰሩ ተስፋ እንደሚያደርግም መንግስት ገልጿል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version