Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ዜለንስኪ የፊት ለፊት ውይይት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱን ሞስኮ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እና ዩክሬን በኢስታንቡል ባካሄዱት የሰላም ድርድር መሰረት ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ዘለንስኪ የፊት ለፊት ውይይት ለማድረግ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ሞስኮ አስታወቀች፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ድርድር ፕሬዚደንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶኻን በተገኙበት በቱርክ ኢስታምቡል ዛሬ ተካሄዷል።
የሰላም ድርድሩን ያስጀመሩት ፕሬዚደንት ኤርዶኻን ባደረጉት ንግግር፥ በሰላም ስምምነት አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ አይኖርም ብለዋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው አሳዛኝ የጦርነት ክስተት እልባት እንዲያገኝ እና ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ነው የቱርኩ ፕሬዚደንት ያሳሰቡት፡፡
ይህን አሳዛኝ ክስተት ማስቆም ሁለቱም ወገኖች ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የግጭቱ መራዘም ለማንም የሚጠቅም እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢስታንቡል በሚገኘው የዶልማባቼ ቤተ መንግስት የተካሄደው የሰላም ውይይቱ፥ ጦርነቱን ሙሉ በመሉ ለማቆም ያለመ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡
እንደ አር ቲ ዘገባ ከሆነ፥ በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቅደመ ውይይት ከተደረገ በኋላ ቭሎዶሚር ዘነልስኪ አና ቭላድሚር ፑቲን የፊት ለፊት ውይይት እንዲያደርጉ ሩስያ ፈቃደኛ መሆኗን የሞስኮ ተደራዳሪ ቭላድሚር ሜደንስኪ መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡
ቀደም ሲል የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬን አቻቸው ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የፊት ለፊት ውይይት ሊዘጋጅ የሚችለው በሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች መካከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ብቻ መሆኑን ሞስኮ አስታውቃለች።
ቭላድሚር ሜዲንስኪ ዛሬ በቱርክ የተካሄደው ድርድር ወሳኝ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፥ የልዑካን ቡድኑ ሊያሳካው በፈለገው ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ሃሳቦች ማግኘታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
በመሰረታዊነት ዩክሬን ገለልተኛ ሀገር ሆና ለመቀጠል ቃል መግባቷን እና ምንም ዓይነት ጅምላ – ጨራሽ መሳሪያ ለመታጠቅ እንደማትሞክር የቀረበው ሰነድ እና የስምምነት ሀሳብ ለፕሬዚዳንት ፑቲን የሚቀርብ መሆኑንም ሜደንስኪ ገልጸዋል፡፡
ሜደንስኪ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ኪየቭ አቅራቢያ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ጨምሮ በአንዳንድ የዩክሬን አካባቢዎች ያለው ወታደራዊ ዘመቻ በእጅጉ እየቀነሰ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡
በዩክሬን ተደራዳሪ ልዑካን መሪ ዴቪድ አራካሚያ በበኩላቸው፥ በተደረገው ውይይት ኪየቭ ከበርካታ ሀገራት የደህንነት ዋስትና ትፈልግ ነበር፥ ይህንንም አረጋግጣለች ነው ያሉት፡፡
እንግሊዝ፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ኢጣሊያ፣ ፖላንድ እና እስራኤል ለኬቭ ደህንነት ዋስትና የሚሆኑ ሀገራት መሆናቸውንም ተደራዳሪ አክራሚያ ዘርዝረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version