Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቤንዚን አቅርቦት ችግርን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የተፈጠረውን የቤንዚን አቅርቦት ችግር በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት በአዲስ አበባ ከተማ ባደረገው ቅኝት ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎችን የተመለከተ ሲሆን ፥ “ቤንዚን አልቋል” የሚሉ ፅሁፎችን የለጠፉ ማደያዎችንም ተመልክቷል፡፡

ወረፋ ሲጠብቁ ያገኘናቸው አሽከርካሪዎችም የቤንዚን “አለመኖር” ስራና ኑሯቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በመግለፅ መንግስት ለችግሩ እልባት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ 117 ማደያዎች መኖራቸውን የገለፀው የከተማዋ ንግድ ቢሮ ፥ የቤንዚን እጥረት መከሰቱንና በህገወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ሶስት ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ገልጿል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አደም ኑር በመሰል ህገ ወጥነት ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

የኢትየጵያ ነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የስርጭት ቁጥጥር ዳይሬክተር ደሬሳ ኮቱ ፥ ለችግሩ መከሰት የተለያዩ ምክንያቶችን ያነሱ ሲሆን ፥ የዩክሬን – ሩስያ ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረውን ዓለማቀፋዊ ችግር በቀዳሚነት በመጥቀስ የጅቡቲ መንገድ መበላሸቱና ከጅቡቲ አዲስ አበባ ከሁለት ቀን እስከ ሁለት ቀን ተኩል ይወስድ የነበረው መንገድ አሁን አራት ቀን ድረስ በመውሰዱ መዘግየት መፈጠሩ ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ በበኩላቸው ፥ ከሎጂስቲክስና ከዓለማቀፋዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አሰረድተዋል፡፡

ከባለፈው አርብ ጀምሮ 6 ሚሊየን ሊትር ቤንዚን ከጅቡቲ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቅሰው ፥ እስከመጭው አርብ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ይፈታል ነው ያሉት፡፡

አቶ አህመድ በጊዜያዊነት ችግሩን ለመቅረፍ ከመንግስት ቋት ቤንዚን እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡

ችግሩ በሌሎች ከተሞችም እንደተስተዋለ ያነሱት አቶ አህመድ ፥ ከአዲስ አበባ ከተማ ቀጥሎ ለሁሉም ከተሞች መፍትሄ እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ የቤንዚን አቅርቦት እጥረትን ከሚፈጥሩ የአጠቃቀም ችግር እንዲታቀብም አቶ አህመድ ጠይቀዋል፡፡

በምንይችል አዘዘውና አፈወርቅ እያዩ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version