የሀገር ውስጥ ዜና

ሚኒስቴሩ በሻማ፣ ዘይት ፣ ሳሙና እና ካልሲ ማምረት ሥራ ያሰለጠናቸውን 110 ወጣቶች አስመረቀ

By Meseret Awoke

March 29, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የጀርመን ትብብር ልማት (ጂ.አይ. ዜድ) ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በሻማ ፣ ዘይት ፣ ሳሙና እና ካልሲ ማምረት ሥራ ያሰለጠናቸውን 110 ወጣቶች አስመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ፥ በአዲሱ የሥራ እና ክህሎት የሥራ ስምሪት ተማሪዎች ከትምህርት ተቋማት ሳይወጡ ለሥራ አስፈላጉ የሆኑ ክህሎቶች እንዲያገኙ ለማድረግ እና ከግሉ ዘርፍ ጋር የማስተሳሰር ሂደትን ለመፍጠር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ወጣቶቹም ባለሙሉ አዕምሮ እና ባለወርቅ እጆች በመሆናቸው ታታሪነት መለያቸው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበው፥ የጀርመን ትብብር ልማት እና ሌሎች ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

የስልጠናውን ሂደት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ፥ ከወጣቶቹ 86ቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው እና 24ቱ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች መሆናቸውን አስታውሰው ፥ በ22 ኢንተርፕራይዞች መደራጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለኢንተርፕራይዞቹ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የማምረቻ ቦታ ያመቻቸላቸው ሲሆን ፥ በቀጣይም የብድር እና የማምረቻ መሣሪያ የዱቤ ግዢ የሚፈፀምላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የጀርመን ትብብር ልማት ተወካይ ቤንጃሚን ተድላ ፥ ክህሎት ለወጣቶች ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ፥ የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሰፊ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመሥራት ትብብሩን ያጠናክራል ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ ከዚህ ቀደም የአዋጭነት ዕቅዳቸውን አቅርበው ያስተቹ ሲሆን ፥ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይም የጥቂቶቹ የንግድ ዕቅድ ቀርቧል፡፡

በናሙናነት ለመጀመሪያ ጊዜ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተውጣጥተው ከመጡት ሰልጣኞች 45 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!