አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የወልመል ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 5 ሺህ ሔክታር መሬት ማልማት እንዲችል እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ወልመል የመስኖ ፕሮጀክት 11 ሺህ ሔክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የወልመል ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን በመስክ ተመልክተዋል፡፡
ኢንጂነር አይሻ በወቅቱ የዝናብ ውኃን ብቻ በመጠበቅ በሚደረገው የግብርና ስራ ከድህነት መውጣት እንደማይቻል በመገንዘብ መንግስት ለዘመናዊ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው ቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገነቡት የመስኖ ፕሮጀክቶች የድርቅ ተጋላጭነትን በመቀነስ የአርብቶ አደሩ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
በባሌ ዞን ደሎ መና የአርብቶ አደር ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኘው ወልመል ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የዚሁ አካል እንደሆነም ገልጸው ፕሮጀክቱ የግንባታ ዕቃ አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥመውና በታቀደው ጊዜ ለአገልግሎት እንዲበቃ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዶ ገለቶ በበኩላቸው ÷የፕሮጀክቱ ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከፍተኛ የሰው ኃይልና ማሽነሪዎችን እንቅስቃሴ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወልመል የመስኖ ፕሮጀክት 11 ሺህ ሔክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለውም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፕሮጀክቱ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 5ሺህ ሔክታር መሬት ማልማት እንዲችል እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ ቀሪውን 6ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለማው የግንባታ ምዕራፍ ደግሞ በቀጣይ ዓመት የሚጠናቀቅ ይሆናል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2012 ዓ.ም የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የወልመል ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ22 ሺህ ለሚበልጡ አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!