Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠብቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ይሆን ዘንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠብቅባቸውን አገራዊ ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የኢዜማ እና ኢዴህ ፓርቲዎች ገለጹ ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ለምክክሩ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል ።

በፓርቲው የአገራዊ ምክክር ኮሚቴ ሰብሳቢ እዮብ መሳፍንት፥ ኢዜማ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ኮሚቴ አቋቁሟል፤ ስለ አገራዊ ምክክሩም ግንዛቤ የሚያሳድግ ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል ።

በምክክሩ ሂደት ድርሻ ካላቸው አካላት ጋር በቅርቡ በጋራ ለመስራትና አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማበርከት እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው፥ ፓርቲያቸው ተመሳሳይ ሚና ለመጫዎት ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል።

ምክክሩ ቅንነት በተሞላበት መንገድ እንዲካሄድና አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ወደ ፊት መጥተው ይፈተሹ ዘንድ ፓርቲያቸው ፍላጎት አለው ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የዜጎች ሰላምና ደህንነት፣ የህገ- መንግስትና ሌሎች ጉዳዮች ወደ መድረክ ቀርበው እንዲመከርባቸው እንሰራለን ነው ያሉት ሊቀመንበሩ ።

ለማህበረ ፓለቲካው መበላሸት ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች እንዲታረቁ እና መቀራረብ እንዲፈጠር ፓርቲዎቹ ትኩረት እንደሚሰጡም አስረድተዋል ።

ጠንካራ አገረ መንግስትን እውን በማድረጉ ሂደት ከፓለቲካ ፓርቲዎች የሰከነ እና ቀናነት የተላበሰ አሰራሮች እንደሚጠበቁም ፓርቲዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል ።

በአወል አበራ

Exit mobile version