አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላ ሀገሪቱ በተካሄዱ ውይይቶች ህዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የሚመልሱ እቅዶች ተዘጋጅተው እንዲተገበሩ የብልፅግና ፓርቲ አቅጣጫ ማስቀመጡን በማህበራዊ ገፁ አስታወቀ።
የብልፅግና ፓርቲ በቅርቡ ባካሄደው አንደኛ ጉባዔው ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች አስመልክቶ በመላ ሀገሪቱ ከህዝቡ ጋር ሲያደርግ የነበረውን ውይይት አጠናቋል።
የውይይቶቹን መጠናቀቅ ተከትሎም በዛሬው እለት በማእከል ደረጃ የመድረኮቹን አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተገኙበትና የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በመሩት የዛሬው መድረክ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደር መድረኮች የተነሱ ዋና ዋና ሃሳቦች ተገምግመዋል።
በህዝቡ የተነሱትን የህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ዝርዝር እቅዶች ተዘጋጅተው እንዲተገበሩ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር እንዲገባ ፓርቲው አቅጣጫ አስቀምጧል።