አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶኻን እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀጣዩን የሩሲያ-ዩክሬን ድርድር በቱርክ ኢስታምቡል ለማካሄድ መስማማታቸው ተገለፀ፡፡
የቱርክ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ መሪዎች እሁድ እለት የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን እና ስለ ሩሲያ – ዩክሬን ግጭት ወቅታዊ ሁኔታ እና የድርድር ሂደት መወያየታቸውን አስታውቋል፡፡
በውይይታቸውም ቀጣዩ የሩሲያ እና የዩክሬን የድርድር ሂደት በቱርክ ኢስታምቡል እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን፥ ቱርክ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነት እንዲደረግ እና በአካባቢው ያለው የሰብአዊ ሁኔታ መሻሻል እንዳለበት ገልጸውላቸዋል።
የዩክሬን ተደራዳሪ ልዑካን ቡድን አባል የሆኑት ዴቪድ አራካሚያ ቀጣዩ ዙር የዩክሬን እና የሩሲያ የሰላም ድርድር በሚቀጥለው ሳምንት በቱርክ እንደሚካሄድ ግለጻቸውን ሺንዋ በዘገባው አስነብቧል፡፡
የሩሲያ ተደራራደሪ ቡድን መሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪ በበኩላቸው የፊት ለፊት ድርድሩ በቀጣይ ሳምንት እንደሚደረግ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የዩክሬን እና የሩሲያ ልዑካን ከየካቲት 28 ጀምሮ በቤላሩስ ሶስት ዙር የሰላም ድርድር ያደረጉ ሲሆን አራተኛውን የሰላም ድርድር ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሄደዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!