አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተገቢው ለማስከበር አስቸጋሪ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል ለውጥ ማምጣት መቻሉን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ በተጀመረው መድረክ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው ÷ ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት የህግና ፍትህ ማሻሻያዎችና የዘርፉ ተቋማት ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተገቢው ሁኔታ ለማስከበር አስቸጋሪ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩና በክልል ፍትህ ቢሮዎች በህግና ፍትህ ማሻሻያ ላይ በሚመክረው መድረክ ከተሸሻሉ አዋጆች የሲቪክ ማህበራት፣ የአስተዳደርና የጠበቆች አዋጅ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፣ የጸረ ሽብር አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን አዋጅ እንዲሁም ሌሎችም የህጎች ማሻሻያ የተደረገባቸው አዋጆች ይገኙበታል፡፡
የፍትህ ተቋማት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሙያዊ ነጻነታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩም አበረታች ተግባራት መከናወናቸው ነው የተነገረው።
የዛሬው መድረክ ዓላማም በፌዴራል ደረጃ ሲከናወን የነበረው የህግና የፍትህ የማሻሻል ሥራዎች ክልሎች ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተመቻቸ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
መድረኩ ማሻሻያ ተደርጎባቸው በፌዴራል ደረጃ ተፈጻሚ እየሆኑ ያሉ የህግና የፍትህ ሥራዎች በክልሎች ተግባራዊ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ እንሚፈጥርም ተመልክቷል፡፡
”ምክር ቤቱ ህጎች በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ከትትልና ቁጥጥር ያደርጋል” ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ናቸው።
ምክር ቤቱ የተለያዩ ህጎችን ከማውጣት በተጨማሪ በአግባቡ ተግባራዊ መሆናቸውን በክትትልና ቁጥጥር ስራው ያረጋግጣል ብለዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮችና የክልሎች የፍትህ ቢሮ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
በለይኩን ዓለም