የሀገር ውስጥ ዜና

በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን “ከዒድ እስከ ዒድ ወደ ሀገር ቤት” ጥሪን እንዲሳተፉ ተጠየቀ

By Alemayehu Geremew

March 28, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከዒድ እስከ ዒድ – ወደ ሀገር ቤት” በሚለው ሀገራዊ ጥሪ ላይ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሳተፉ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ጥሪ አቀረቡ፡፡

አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን በመርሃ-ግብሩ ዝግጅት ላይ በጀርመን፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በፖላንድ ሪፐብሊክ ፣ በስሎቫክ ሪፐብሊክ፣ በዮክሬይን፣ በስዊድን ፣ በኖርወይ ፣ በዴንማርክ ፣ እና በፊንላንድ ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ጋር በበይነ-መረብ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ሙሉ ÷ ታላቁ የገና ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ” መርሃ-ግብር በስኬት መጠናቀቁን አስታውሰው ፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚያኮራ መልኩ በወሳኝ ወቅት ለሃገራቸው ያላቸውን ድጋፍ እና ፍቅር በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡

“ከዒድ እስከ ዒድ ወደ ሀገር ቤት ጉዞ” በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በድጋሚ የቀረበ ጥሪ መሆኑን ለተሣፊዎቹ አብራርተው፣ ጉዞው ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶች ዕሴትና የአብሮነት ባለቤት መሆንዋን ለዓለም የምናሳይበት ነውም ብለዋል።

“ከዒድ እሰከ ዒድ-ወደ ሀገር ቤት” በሚል መርህ የሚደረገው ዝግጅትም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለዉና አንድነታችንን የሚያጠናክር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት በመሄድ በዝግጅቱ እንዲሳተፉ አምባሳደር ሙሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በበይነ መረብ በተካሄደው ዉይይት የተሳተፉት የዳያስፖራ አባላት እንዳሉት ዝግጅቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነት ያላቸው ሕዝቦች ተፈቃቅረው እና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን በድጋሚ ለዓለም የምናሳይበት ነው ብለዋል።

በመጀመሪያው ጉዞ የነበሩትን መልካም ጎኖች በማጠናከርና የታዩትን ክፍተቶች በማረም ሁሉም መረባረብ እንደሚገባ ተሣታፊዎቹ መናገራቸውን በጀርመን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡