የሀገር ውስጥ ዜና

51ኛው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው

By Alemayehu Geremew

March 28, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በሻምፒዮናው ከሰባት ክልሎች ፣ ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና ከ24 ክለቦችና ተቋማት የተውጣጡ 1 ሺህ 33 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በሴቶች የአሎሎ ውርወራ የፍፃሜ ውድድር የመከላከያዋ ዙርጋ ኡስማን ስታሸንፍ መርሃዊት ፀጋዬ እና አመለ ይበልጣል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መከላከያ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡

በርቀቱ ዙርጋ ኡስማን 13 ነጥብ 56 ሜትር በመወርወር ስታሸንፍ ፣ መርሃዊት ፀጋዬ ደግሞ 12 ነጥብ 24 ሜትር በመወርወር የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች ፤ አመለ ይበልጣል ደግሞ 12 ነጥብ 16 ሜትር በመወርወር 3ኛ ወጥታለች፡፡

የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ክችማን ኡጁሉ አሸናፊ በሆነበት የወንዶች ስሉዝ ዝላይ ዶል ማች እና በቀለ ጅሎ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።

ክችማን ኡጁሉ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊ የሆነው 16 ነጥብ 3 ሜትር ስሉስ በመዝለል ሲሆን ፣ ዶል ማች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 15 ነጥብ 79 ስሉስ በመዝለል እንዲሁም በቀለ ጅሎ ከኦሮሚያ 15 ነጥብ 54 ስሉስ በመዝለል የሁለተኛነትንና ሦስተኛነትን ደረጃ አግኝተዋል፡፡

በሌላ መርሃ -ግብር የ100፣ 400 እና 800 ሜትር በሁለቱም ፆታ የማጣሪያ ውድድሮች እየተከናወኑ ነው።

የሻምፒዮናው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ከ8 ሠዓት 30 ጀምሮ ሲካሄድ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ይጠበቃል።

ከውድድሩ በ22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች እንደሚመረጡ ተመላክቷል፡፡

በሐዋሳ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ የሚካሄደው ውድድር እስከ መጋቢት 24 እንደሚቆይም ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በታሪኩ ጉታ