Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለልዩ ዘመቻዎች ኃይል እና ለሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል አመራሮች እና አባላት ሜዳይ እና እውቅና ተሠጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከህግ ማስከበር ህልውና ዘመቻ እስከ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተካሄደው ሀገር የማዳን ዘመቻ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል እና የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል ውጤታማ የተልዕኮ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለፁ።

ለልዩ ዘመቻዎች ኃይል እና ለሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል አመራሮች እና አባላት በተዘጋጀው የሜዳይ እና የእውቅና አሰጣጥ መርሀ ግብር ላይ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ የመሰረታዊ ኮማንዶ አባላትም ተመርቀዋል።

በዕለቱም የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የተዘጋጁ ሽልማቶችን አበርክተዋል።

በብላቴ ልዩ ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከል በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ፕሮግራሙን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ÷ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል እና የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል የተለያዩ ተልዕኮዎችን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ከህግ ማስከበር ህልውና ዘመቻ እስከ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተካሄደው ሀገር የማዳን ዘመቻ በተካሄዱ ወጊያዎች አንጸባራቂ የጀግንነት ተጋድሎ መፈፀማቸውን ገልፀዋል።

የዕለቱ የኮማንዶ ተመራቂዎች በማዕከሉ ቆይታቸው በቀጣይ የሚጠብቃቸውን ተልዕኮ ግምት ውስጥ ያስገባ በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የተደገፉ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን መከታተላቸውን ተናግረዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ÷ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል እና የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል በተሰማሩባቸው የተልዕኮ ቀጠናዎች ሁሉ ለህዝቡና ለሠራዊቱ የሞራል ምንጭ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ቶይታችሁ የቀሰማችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር እና የጀግኖችን ፈለግ በመከተል እራሳችሁን ተከታታይነት ባለው ሥልጠና ማብቃት ይጠብቃችኋል ብለዋል።

ተመራቂ መሠረታዊ ኮማንዶዎች ወታደራዊ ሥልጠናቸውን በብቃት በማጠናቀቃቸው እና የድል አድራጊዉ ሠራዊት አባል በመሆናቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version