አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮች በዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት ላይ በሞሮኮ ራባት ውይይት አካሂደዋል፡፡
በተካሄደው የዓለም አቀፉ የፍልሰት ስምምነት መድረክ ÷በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ እና ከማስፈጸም አንፃር አመርቂ ውጤት ያሳዩ ሀገራት ተመርጠዋል፡፡ የሀገራት ሚኒስትሮችም ውይይት አካሂደዋል ነው የተባለው፡፡
በዚህ የሚኒስትሮች ውይይት ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው ፥ በበይነ መረብ የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
በንግግራቸውም የሰዎች እንቅስቃሴ ተፈጥሮዋዊ መሆኑን እና ዜጎቻችንም ሆኑ የሌሎች ሀገራት ዜጎች በፍልሰት ሂደት ውስጥ መብት እና ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ከማድረግ አንፃር ሁሉም ሀገራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያም ለህጋዊ፣ መደበኛ እና ሥርዓቱና ደኅንነቱ ለተጠበቀ የሰዎች እንቅስቃሴ እውን መሆን ያላትን ቁርጠኝነት እና እያከናወነች ያለውን ዋና ዋና ተግባራት ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል፡፡
በመድረኩ የተለያዩ የዓለም ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን ፥ ከአፍሪካ ጋና፣ ቻድ፣ ግብጽ፣ ጊኒ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እንዲሁም ሞሮኮ ሲሳተፉ ፥ ከተቀሩት ዓለም ሀገራትም ካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ፖርቹጋል፣ ኢንዶኒዢያ፣ ፊሊፒንስ፣ ባንግላዴሽ እና ሌሎች ሀገራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
መድረኩን የስብሰባው አዘጋጅ ሀገር የሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፉ ፍልሰት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቬቶሪኖ መምራታቸውን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡