የሀገር ውስጥ ዜና

ሰብዓዊ ድጋፉን ለማፋጠን መንግስት ያሳለፈው የግጭት ማቆም ውሳኔ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመልካምነት የታየ ነው – የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን

By Melaku Gedif

March 26, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ሰብዓዊ ድጋፉን ማሳለጥን መሠረት ያደረገው የግጭት ማቆም ውሳኔ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመልካምነት የታየ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ የዜጎችን ህይወት ቅድሚያ የሰጠው የመንግስት ውሳኔ ሀገራት በበጎ የተመለከቱትና የተቀበሉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ሰብዓዊ ድጋፉን ለማፋጠን የግጭት ማቆም ውሳኔ በሌላኛው ወገን ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅም ነው ያብራሩት።

መንግስት እርምጃው ወደ ውጤት እንዲቀየር የተሟላ ቁርጠኝነት እንዳለውም አረጋግጠዋል ።

በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰበሰቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ለተጨማሪ ድጋፎች መንግስት የሚያደርገው ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ድጋፉ በመንግስት ጥረት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መላው ኢትዮጵያውያንም እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

ግጭቱ ጉዳት ባደረሰባቸው የሰሜን ወሎና ዋግኸምራ ዞኖች 117 ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸው÷ጊዜያዊ መቆያዎችን በማቋቋም ድጋፍ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ በተባለ ቦታ በተቋቋመ ጊዜያዊ መጠለያ 8 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

በጦርነቱ ምክነያት ከአማራ ክልል ብቻ 1 ነጥ 4 ሚሊየን ያህል ዜጎች ተፈናቅለው ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ከእነዚህ ውስጥ 1ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከደረሰው ችግር አንፃር ቀውሱ በቶሎ ያላገገመ በመሆኑ በአማራ ክልል 11 ሚሊየን የሚሆኑት የምግብ ዋስትናቸው ያልየረጋገጠ ዜጎች በመኖራቸው የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

በአፋርም አንዲሁ 1ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ድጋፍ ለማድረስም ሲሰራ ቆይቷል ፣ተጠናክሮም ቀጥሏል ነው ያሉት።

ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ቦረናና ምስራቅ ባሌ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ዞኖች የዕለት ደራሽ ድጋፍ ለሚያስፈለልጋቸው ድጋፍ ለማቅረብ እና የውሃ አቅርቦትንም ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የብልፅግና ጉባኤን ተከትሎ በመላ አገሪቱ የተካሄዱ ምክክሮችም ህዝቡ በንቃት የተሳተፈባቸውና ስኬታማ የነበሩ መሆናቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል።

አቅጣጫዎቹን በበቂ እና አካታች በሆነ መንገድ ለመተግበር እድል የሚሠጡ እንደነበሩና ህዝቡም የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኝነቱን ያሳየባቸው መሆናቸውን ነው የገለጹት ።

ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም ጭምር ኢትዮጵያን በእጅጉ ለመጉዳት የተዘጋጀው የኤፍ አር6600 ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ የመንግስትን ለሰብዓዊነት የተደረጉ ጥረቶችን ከግምት ያላስገባና አጥፊውን ወገን ያልለየ በመሆኑ እንዳይፀድቅ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ጥረት እንዲጠናከርም ጥሪ አቅርበዋል።

በሃብታሙ ተክለስላሴ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ! ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!