አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለህዝብ እንዲከፋፈል የመጣን ስኳር ለግልጥቅማቸው ለማዋል የሞከሩ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ሰራተኞቹ በየካ ክፍለ ከተማ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለህዝብ እንዲከፋፈል የመጣን ስኳር ለህጋዊ ነጋዴዎች የሚወጣ ድርሻ በማስመሰል ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ሲያሥጭኑ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡
በክፍለ ከተማው ወረዳ 8 ቁጥር 7 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር የሽያጭ ኃላፊ፣ ገንዘብ ተቀባይና የግምጃ ቤት ኃላፊን ጨምሮ አምስት ግለሰቦች ተጠርጣሪ ሆነዋል፡፡
መጋቢት13 ቀን 2014 ዓ.ም ግለሰቦቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደምልካም አጋጣሚ በመጠቀም መንግሥት ለህዝብ እንዲከፋፈል ያመጣውን ስኳር በህጋዊነት ለሚሰጣቸው ነጋዴዎች የሚወጣ በማስመሰል ለግል ጥቅማቸው 15 ኩንታን ስኳር መኪና አስመጥተው ሲጭኑ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ ከነመኪናው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ግለሰቦቹ በወረዳው ሸማቾች ከሽያጭ ሃላፊነት ጀምሮ ገንዘብ ተቀባይና የግምጃ ቤት ኃላፊው የወንጀሉ ተሳታፊ መሆናቸው ለወንጀሉ መፈፀም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ ተጠርጥረው በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
መንግስት በወቅታዊ ሁኔታ የተከሰተውን የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት በመገንዘብ በሸማች ሱቆች አማካኝነት ለህዝብ እንዲዳረስ የሚያመጣቸውን ሸቀጣ-ሸቀጥ ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ግለሰቦች እየተበራከቱ ስለመጡ÷ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመከታተል አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆን ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡