አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለዘመናት የቅራኔ ምክንያት የነበሩ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ሁሉም ህብረተሰብ በንቃት እንዲሳተፍ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሰላም እናቶች ጠየቁ።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የመጀመሪያውን የትውውቅ ሁነት ከሀይማኖት አባቶች ፤ ከሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች የሰላም እናቶች ጋር ትናንት ማድረጉ ይታወቃል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ያነጋገራቸው አባቶች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ በህዝቦች መካከል የነበሩ ቅራኔዎችን በውይይት ለመፍታት ህብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ አለበት፡፡
ለዚህም በአገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ይህንን ታሪካዊው እድል መጠቀም ይገባል ነው ያሉት ፡፡
አካታችና አሳታፊ ሂደትን እንደሚያልፍ በሚጠበቀው የምክክር ስራ ውስጥ ሁሉም በንቃት ለሀገሩ ሰላም ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው ለውይይት የሚሆኑ ሀሳቦችን ግብአት የማሰባሰብና ኮሚሽኑን የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
የምክክር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የማመቻቸት ሀላፊነታችንን እንወጣለን ያሉት የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ፥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ እንዲሳተፉም መልእከት አስተላልፈዋል ።
በሀይለየሱስ መኮንን