Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አንድ ሚሊየን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው የደህንነት ካሜራዎችን ሰርቀዋል የተባሉ ግለሰቦች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ ሚሊየን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው ለደህንነት አገልግሎት የሚገጠሙ ካሜራዎችን የሰረቁ ተጠርጣሪዎችን እና ንብረቶቹን የገዙ ግለሰቦችን እጅ ከፍንጅ ይዞ ንብረቶቹን ማስመለሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በለሚኩራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኘው ሲ.ጀ.ሲ.ኦ.ሲ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 996 ሺህ ብር የሚያወጡ 41 ለደህንነት አገልግሎት የሚውሉ ካሜራዎችን እና 36 የካሜራ መደገፊያዎችን የሰረቁ ተጠርጣሪዎችንና ንብረቶችን የገዙ ሁለት ግለሰቦች ይዞ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የስርቆት ወንጀሉን የፈፀሙት ሁለት ግለሰቦች ከዚህ ቀደም በድርጅቱ ውስጥ በቀን ሰራተኝነት ሲሰሩ እንደነበር እና የድርጅቱን መግቢያና መውጫ ካጠኑ በኋላ የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ወንጀሉን እንደፈፀሙ በምርመራ መረጋገጡን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ግለሰቦቹ ወንጀሉን በፈጸሙ በአስረኛው ቀን ድርጅቱ ንብረቶቹን መሰረቁን ለፖሊስ ሪፖርት እንዳደረገና ፖሊስም በቴክኖሎጂ በመደገፍ ባደረገው ክትትል የወንጀሉ ሪፖርት በደረሰው በሦስተኛው ቀን ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ንብረቶቹን በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሮባ ዳቦ ቤት አካባቢ ከሚገኙና ንብረቱን ከገዙ ሁለት ግለሰቦች እጅ አስመልሶ ምርመራውን መቀጠሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version