አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አገልግሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በጤና ኬላዎች ላይ የወሊድ አገልግሎትን ጨመሮ ሌሎች መሰረታዊ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽ ፕሮግራም አገልግሎት በጅማ ዞን ሰቃ ጮቆርሳ ወረዳ ነው ያስጀመሩት።
ዶክተር ሊያ በሰጡት ማብራሪያ፥ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገውና ላለፉት 16 አመታት ሲተገበር የቆየው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በሀገሪቷ በጤና ዘርፍ በተመዘገበው ስኬት ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 100 የሁለተኛ ትውልድ ጤና ኬላዎች እየተገነቡ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ሊያ፥ ተቋማቱ የወሊድ አገልግሎትን ጨመሮ ሌሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶ/ር ኩሻ ቦሎኮ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል 36 የሁለተኛ ትውልድ ጤና ኬላዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ገልፀው፥ የህብረተሰቡን ጤና ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮ በበኩላቸው፥ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በዞኑ ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ፥ መንግስት የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀው፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን የሁለተኛ ትውልድ ጤና ኬላ አጠናቀው ላስመረቁ የሰቃ ጮቆርሳ ወረዳ ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በሙክታር ጠሃ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!