አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን የነዳጅ እና የጋዝ ምርት የአገር ውስጥ መገበያያ በሆነው ሩብል ወይም በቢት ኮይን ልትሸጥ እንደምትችል አስታውቃለች፡፡
በሩሲያ ፓርላማ የኢነርጅ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ፓቬል ዛቫልኒ እንደገለጹት÷የአሁን ላይ በአገሪቱ በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት በሞስኮ የተፈጥሮ ጋዝን በዶላር ወይም በዩሮ መሸጥ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
በዚህ ሳቢያም ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን የነዳጅ እና የጋዝ ምርት የአገር ውስጥ መገበያያ በሆነው ሩብል ወይም በቢት ኮይን ልትሸጥ እንደምትችል ነው የገለጹት፡፡
በአንጻሩ ለሩሲያ ወዳጅ ለሆኑ አገራትን ማለትም÷ለቱርክ እና ለቻይና የተሻለ አማራጭ የክፍያ መንገዶች እንደሚመቻቹ ም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
ፓቬል ዛቫልኒ የሩሲያው ሩብል እና የቻይናው ዩዋን እንደመገበያያ ለመጠቀም ቀደም ብለው ለቻይና ሀሳብ ማቅረባቸውን በመጠቆም÷ ከቱርክ ጋርም በሊይሬ እና በሩብል ግብይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከወዳጅ አገራት ጋር በምናደርገው ግብይት ቢት ኮይንንም እንደ አማራጭ መጠቀም እንችላለን ሲሉ ሊቀመነበሩ መግለጻቸውን ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ወዳጅ ያልሆኑ” አገራት የሞስኮን የነዳጅ ዘይት ምርት በሩብል እንዲገዙ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ጦርነቱን ተከትሎ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት አባላ ሀገራት የተጣሉ ማዕቀቦች በሩሲያ ሩብል ላይ ጫና በመፍጠር የኑሮ ውድነቱ ከፍ እንዲል ማድረጉን መረጃዎች ያመላክታሉ።