Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ክልሎች ጤናማ ፉክክር በማድረግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅማቸውን ሊጠቀሙ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት አተገባበር ላይ የሚመክር ሀገራዊ የቅንጅት ዲፕሎማሲ መድረክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በዘርፉ ያጋጠሙ ማነቆዎችና መፍትሄዎቻቸውን እንዲሁም በፖሊሲ አማራጮች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን፥ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ የሚያዋክቡትን ለማሸነፍና የወጪና ገቢ ንግድ ምጣኔን ለማስተካከል የሚያስችሉ አሰራሮች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ የሚያስወጡ ግብይቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የንግድ ምጣኔ ሚዛኑን ለማስተካከልም መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶች ሲመጡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንደ ክልሎቹ ነባራዊ ሁኔታ መፍታት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተነስቷል።

ክልሎች ከቀደመ መልካቸው በተጨማሪ ኢንቨስትመንት መሳብና ጤናማ ፉክክር በማድረግ አቅማቸውን መጠቀም እንደሚገባ ተነስቷል፡፡

በዘርፉ የአፋርና ሶማሌ ክልሎች አበረታች ለውጥ ማሳየታቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው መድረክ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን ፥ በኢንቨስትመንት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራና የተናበበ ቅንጅታዊ አሰራርን መተግበርና ለገጠሙ ችግሮችም መፍትሄን ማመላከት እንደሚገባም ተነስቷል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ÷ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን፣ የኢኮኖሚ ፈተናዎችንና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የኢንቨስትመንት ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

የፀጥታ ችግር፣ የአሥፈፃሚ አካላት የአቅም ማነስና የግንዛቤ መዛባት፣ የመሬት አቅርቦትና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች፣ የመሠረተ ልማት ጉድለቶች፣ የኢንቨስትመንት ዑደት ችግሮች በሀገሪቱ ቀጥተኛ ኢንቨስመንት ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውንም አንስተዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የተዛባ ግንዛቤ መኖር እና ከላይ የተጠቀሱት ተግዳሮቶች ዘርፉን እያጠለሹ እንደሆነና የባለሐብቶችን ተሳትፎ እየቀነሱ እንደሆነም ነው ያመለከቱት፡፡

ኢንቨስትመንትን ማጠናከርና ችግሮችን መፍታት የሁሉም ባለድርሻዎችን ትኩረት የሚፈልግ መሆኑም በመድረኩ ተጠቁሟል።

በአፈወርቅ እያዩና ታሪኩ ለገሰ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version