አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ገጽታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በሞስኮ የአፍሪካ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር አንድሬይ ማስሎቭ ተናገሩ፡፡
ዳይሬክተሩ ከአር ቲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት÷ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩ ባሻገር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአህጉሪቷ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አንዲገታ አድርጓል፡፡
የሩሲያ መንግሥት የአገር ውስጥ ገበያን ለማረጋጋት ወደ ውጭ በሚወጡ ምርቶች ላይ የጣለው ማዕቀብ እና የወሰዳቸው ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎች በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸውም ገልፀዋል።
ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2020 ባሉት ጊዜያት ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ አፍሪካ ከሚያስገቡት አጠቃላይ ስንዴ 25 በመቶውን ያቀረቡ ሀገራት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
ሰለሆነም ወደ ውጭ በሚላከው የስንዴ ምርት እገዳ መጣሉ ፣ በዩክሬን የስንዴ ልማት ወቅት መስተጓጎሉ እና በጥቁር ባህር መስመር ያለው የትራንስፖርት መስመር ችግር በቀጣይ በአፍሪካ ላይ መዘዝ ሊያመጣ ይችላል ነው ያሉት፡፡
በዲፕሎማሲያዊ ረገድ አፍሪካ በግጭቱ ዙሪያ ገለልተኛ መሆንን መርጣለች ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ከ 54 የአፍሪካ ሀገራት 26ቱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ለማውገዝ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ አለመደገፋቸውን አብራርተዋል፡፡
አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ብሩንዲ፣ ዚምባብዌ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ደቡብ ሱዳን በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ሀገራት መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ኤርትራ የመንግስታቱን ድርጅት የወሳኔ ሃሳብ ስትቃወም ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ካሜሩን፣ ሞሮኮ፣ ቶጎ፣ እስዋቲኒ እና ኢትዮጵያ ድምጽ ያልሰጡ ሀገራት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ግብፅ የተባበሩት መንግስታትን የውሳኔ ሃሳብ ብትደግፍም ከሩሲያ ጋር ትብብር እያደረገች መሆኑን እና በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦችን የተቀላቀለ አንድም አፍሪካዊ ሀገር እንደሌለ መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!