Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጽጽቃ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ60 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በአራት የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን÷ ከእነዚህ መካከል በዝቋላ ወረዳ የጽጽቃ መጠለያ ጣቢያ አንዱ ነው።
በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ሥር በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ከ18 ሺህ 300 በላይ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ።
ከተፈናቃዮቹ መካከል አብዛኛዎቹ ሕፃናት፣ እናቶች እና አቅመ ደካሞች የሚገኙበት ተመላከተ ሲሆን÷ በአዳራሾች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ተጠልለው ይገኛሉ።
ተፈናቃዮቹ እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ወረራ ቤታቸው እና ንብረታቸው ወድሞና ተዘርፎ በባዶ እጃቸው ነው ወደ ጽጽቃ መጠለያ የገቡት።
በመጠለያ ጣቢያው ከሶስት ወር በላይ ቢሆናቸውም በቂ የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ በፍጥነት ባለመድረሱ በርሃብ ችግር ውስጥ እንደወደቁ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።
በርካታ ተፈናቃዮች በአንድ አዳራሽ ውስጥ በመኖራቸው ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መጋለጣቸውንም ነው የተናገሩት።
የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ሕፃናት፣ ነብሰጡር እና አጥቢ እናቶች ምንም አይነት አልባሳት እና ፍራሽ በሌለበት ባዶ ክፍል ላይ ተኝተው ተመልክቷል።
የዝቋላ ወረዳ አደጋ መከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ወርቁ ሳህሊ÷ በወረዳው የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ18 ሺህ በላይ መድረሳቸውን ጠቁመው÷ ለተፈናቃዮቹ በተቆራረጠ መንገድ ድጋፍ ቢደረግም ካለው የተፈናቃይ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ተፈናቃዮቹ ለችግር ተጋልጠዋል ብለዋል።
ወረዳው ባለበት የጸጥታ እና የትራንስፖርት ችግር ምክንያት ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ የደረሱ ድጋፎች በትክክል ወደ መጠለያ ጣቢያው ተደራሽ አለመሆናቸውንም አንስተዋል።
በወረዳው ያለውን ችግር ለመፍታት በሽብር ቡድኑ የተያዙ አካባቢዎችን ነጻ በማድረግ ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት መመለስ ካልተቻለ ችግሩ ከዚህም ሊከፋ እንደሚችል አቶ ወርቁ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version