አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የበልግ ወቅት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 46 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ ገለጹ፡፡
ዳይሬክተሩ ትልቁን የበልግ የምርት ድርሻ የሚሸፍኑት የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ዘር ወደ አካባቢዎቹ መሰራጨቱንም አስታውቀዋል፡፡
የዓመቱ የዘር አቅርቦት የሚዘጋጀው ከመኸር ጋር አንድ ጊዜ በመሆኑ ምንም አይነት የግብአት አቅርቦት ችግር እንደማይኖርም ነው ያስታወቁት፡፡
ዘር የማከፋፈል፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ እንዲሁም በየአካባቢዎቹ ዘር የማከፋፈል ሥራ መሠራቱም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጅ ኢኒስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ÷ አሕመዲን አብዱልከሪም በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ኢንስቲቲዩቱ የዘንድሮው የበልግ ወቅት ዘግይቶ እንደሚገባና መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ ሁኔታ እንደሚገኝ ትንበያ መስጠቱን ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ በተለይ በደቡብ፣ መካከለኛውና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በአንፃራዊነት ጠንካራ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል።
የማሳ እና የተለያዩ የአጭርና የረጅም ጊዜ በበልግም ሆነ በመኸር ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችን ለመዝራት አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ቀድመው ለተዘሩ የተለያዩ ሰብሎች ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ዘር ለመዝራት የዘገዩ አካባቢዎችም አጋጣሚውን እንደመልካም ዕድል በመጠቀም እንዲዘሩ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።