አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾመዋል፡፡
የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት አቶ ግርማ ዋቄ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በገዛ ፈቃዳቸዉ ስራ መልቀቃቸውንና አዲስ የተመሰረተውን ቦርድ አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም አቶ ተወልደ ላለፉት 6 ወራት ህክምናቸውን በአሜሪካ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ጠቁመው÷ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ትናንት የተቋቋመው አዲሱ ቦርድ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በምስጋና አሰናብቷቸዋል ብለዋል።
ይህን ተከትሎም ቦርዱ አቶ መስፍን ጣሰውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ አድርጎ መሾሙን ተናግረዋል።
አቶ መስፍን ጣሰው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ፣ የጥገናና ኢንጂነሪንግ፣ እንዲሁም ኦፕሬሽን ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።
ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮም የአየር መንገዱ ስራ አመራር ቦርድ ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ከዚያ በመቀጠል የኢትዮጵያ አየር መንገድ 40 በመቶ ድርሻ ያለበትን አስኪ አየር መንገድን ዋና ስራ አስፈፃሚ በመሆን በመምራት ላይ ነበሩ።
ከዚህ ባለፈም እስከትናንት ወዲያ በስራ ላይ ያለው ቦርድ በአዲስ አመራር መተካቱን አቶ ግርማ ዋቄ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ፡-
አቶ ተክለወልድ አጥናፍ ፣
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣
ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣
አቶ ታደሰ ጥላሁን እና
ሁሉንም ሰራተኛና ማኔጅመንት የሚወክሉና በሰራተኞች ተመርጠዉ የቦርድ አባላት የሚሆኑት እስከሚተኩ ድረስ
አቶ ረታ መላኩ
አቶ አለማየሁ አሰፋ
የአዲሱ ቦርድ አባላት ሆነው ተሰይመዋል ።
በጸጋዬ ወንደወሰን
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!