የሀገር ውስጥ ዜና

በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በደራሽ ውሃ አደጋ ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ የ7 ሰዎች ህይወት አለፈ

By Melaku Gedif

March 23, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በብላቴ ወንዝ ፏፏቴ ተብሎ በሚጠራበት አከባቢ በድንገተኛ የደራሽ ውሃ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡

በደራሽ ውሃው ከተወሰዱት ሰዎች መካከል ነፍሰ ጡር እናት እንደሚገኙበት ነው የተገለፀው።

በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 4 ሰዓት አከባቢ በቁሊቶ ከተማ ገበያ ውለው ወደ ቤታቸው ለመመለስ ወንዙን በማቋረጥ ላይ ሳሉ ድንገተኛ የደራሽ ውሃ አደጋ መከሰቱ ነው የተገለጸው።

ለአደጋው የተጋለጡ ሰዎችን ህይወት ለማስተረፍ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ ቢያድርግም የደራሽ ውሃው ግፊት ከፍተኛ በመሆኑ አንድንም ሰው በህይወት ማትረፍ አልተቻለም ተብሏል።

በአደጋው ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስክሬን እስካሁን ያልተገኘ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት መግለጹን ከሀላባ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ! ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!