Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በህብረተሰቡ የተነሱ የልማት ጥያቄዎች የጋራ ጥያቄዎች በመሆናቸው ችግሮቹ የሚፈቱበትን አማራጭ በመከተል እንሰራለን- ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህብረተሰቡ የተነሱት የመልማት ጥያቄዎች የጋራ ጥያቄዎች በመሆናቸው ችግሮቹ የሚፈቱበትን አማራጭ በመከተል እንደሚሰራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተደድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።
 
በብልጽግና ፓርቲ 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የህዝብ የውይይት መድረክ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙት ተካሂዷል፡፡
 
በመድረኩ በአካባቢያችን ያልተፈቱ የመሰረተ ልማት ችግሮች ሊቀረፉልን ይገባል ሲሉ የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
 
አዲሱ ክልል በማግለል ፖለቲካ ለዘመናት ተጠቅቶ እኩል መልማት ያልቻለ መሆኑን ም ነው ነዋሪዎቹ ያነሱት ።
 
በክልላችን የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የሪፈራል ሆስፒታል እና የቴሌ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ገና የሚቀር በመሆኑ ይህንን ለማሟላት ምን የታሰበ ነገር አለ በማለት ጠይቀዋል።
 
ከ35 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየም ተጠናቅቆ ወደ ስራ አለመግባት፣ የቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
 
ከዞኖች ጋር የሚያገናኙ የአስፓልት መንገድ ስራዎች አለመጀመር፣ በጋዎታ ወረዳ ቆንዳ አካባቢ የሸንኮራ አገዳ ልማት ጥናት ተግባራዊ አለመሆን፣ አንዳንድ ሚዲያዎች ህዝቡን ከሚያጋጩ ተግባራት በመውጣት የህዝብን አንድነትና ወንድማማችነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
 
በውይይቱም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ችግር መቼ ይፈታል?፣ የትግራይ ክልል ህዝብ ጉዳይስ እንዴት አየሆነ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
 
ለተነሱት ጥያቄዎች ከመድረክ መሪዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን÷ በመሠረተ ልማት የተጀመሩ ስራዎች እውን እንዲሆኑና ህብረተሰቡም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ይሰራልም ተብሏል።
 
ከክላስተር አደረጃጀት አኳያ ለተነሳው ጥያቄ ጉዳዩ ከህገ መንግስት ጋር የሚያጋጭ ምንም ምክንያት አንደሌለውና ክልሎች በራሳቸው የከተሞችን ቁጥር መወሰን እንደሚችሉ፤ ይህም ቢተገበር ለሌሎች ክልሎች ሞዴል እንደሚሆን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ሰማ ጥሩነህ አብራርተዋል።
 
ህዝብን እንደህዝብ በማዳመጥ የሚያነሱትን ሀሳብ በመቀበል በመግባባት ችግሮችን በመፍታት እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም በመድረኩ ተገልጿል።
 
የትግራይ ክልል ህዝብ ውክልና እንዲኖረው ብልጽግና አካታች በመሆኑ የራሱ ተወካይ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥና በተለያዩ የመንግስት ኃላፊነቶች እንዲካተቱ በማድረግ የህዝቡን ህልውና ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ሰማ ተናግረዋል።
 
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተደድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ÷የብዝሃ ማዕከላትን በሚመለከት ካለፈው አደረጃጀት ትምህርት ወስደን፣ የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ቀምረን፣ ፍትሐዊ የከተሞች ዕድገት፣ የሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና የአገልግሎት አሰጣጥ በሚያሳልጥ መልኩ እንዲደራጅ ህጋዊ ዕውቅና የተሰጠው መሆኑን አውስተዋል።
 
ለዚህ መሳካትም ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
በህብረተሰቡ የተነሱት የመልማት ጥያቄዎች የጋራችን ጥያቄዎች በመሆናቸው ችግሮቹ የሚፈቱበትን አማራጭ በመከተል እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል ።
Exit mobile version