የሀገር ውስጥ ዜና

መንግስት ዘላቂ ሠላምን በማስፈን ለኑሮ ውድነት መፍትሔ እንዲሰጥ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

By Meseret Awoke

March 23, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ዘላቂ ሠላምን ከመገንባት ጎን ለጎን ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ እንዲሰጥ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔዎች፣ አቅጣጫዎችና አቋሞች ዙሪያ ከአሶሳ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ባለፉት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ስርዓት “አጋር” በሚል አግላይ አሠራር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፖለቲካውም ሆነ በልማቱ በደል እንዲደርስበት አድርጓል ብለዋል፡፡

ሃገርን ለማፍረስ ከተነሳው ሕወሃት ጋር የተደረገው ጦርነት በድል ቢጠናቀቅም አሁንም ድረስ የህብረተሰቡን ሠላም የሚነሱ ተላላኪዎች መኖራቸውን ጠቁመው፥ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ሌላው የህብረተሰቡ ፈተና መሆኑንም አንስተዋል፡፡

መንግስት በህወሓት ተላላኪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ዘላቂ ሠላምን ከመገንባት ጎን ለጎን በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ፈተና ለሆነው የኑሮ ውድነት መፍትሔ እንዲሰጥ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡

በፓርቲው ስር ሆነው ሌላ ዓላማ ባላቸው አመራሮችና አባላት ላይ የተጀመረው የማጥራትና እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ፥ በለውጡ ሂደት ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ሆና የተለያዩ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ገልጸው ይህም በአብሮነት ከተደጋፍን ወደፊት የበለጠ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ዘላቂ ሠላምን የመገንባት ጉዳይ ቀዳሚ የመንግስት ትኩረት ነው ያሉት አቶ አሻድሊ ፥ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር የበለጠ በመቀናጀት በቀጣይ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በተለይም በመተከል ዞን በሽፍታ መልክ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ባሻገር በተለያየ ጊዜ ከጎረቤት ሃገራት ሾልከው የሚመጡ ተላላኪዎች እያደረሱ ያለውን ጥቃት ለማስቆም እንደሚሠራ ጠቁመው ፤ በክልሉ ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ላይ አጸያፊ ተግባር የፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የክልሉ መንግስት ጽኑ አቋም እንዳለውም አመላክተዋል፡፡

ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት የሆኑ ሰው ሰራሽ ችግሮችንና አሻጥሮችን ለመከላከል መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ በመግለጽም፥ ከዚህ ጎን ለጎን ማሳዎችን በሙሉ አቅም ማልማትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ መፍትሄ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው ፥ ብልጽግና ፓርቲ ዘላቂ ሠላምን ከመገንባት ጀምሮ ለህብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቁመው ፥ ለመፍትሔዎቹ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁላችንም እኩል ነን ያሉት ዶክተር አብርሃም ፥ በመከፋፈል አገዛዝ የትም መድረስ አይቻልም ብሎ የታገለ እና ፍሬ ያፈራ ፓርቲ በመሆኑ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመፈጸም በጽናት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የጸጥታ ችግርን በዘላቂነት የመፍታት ተግባር ከመከላከያ ሠራዊት ባለፈ የሕዝብ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን ፥ ሌባ እና ሽፍታ የሚያቅፍ ነዋሪ ካለ ሠላምን መገንባት አይቻልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!