አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ቴወድሮስ አድሃኖም ከጤና ጉዳዮች ይልቅ የግል የፖለቲካ አቋማቸው ትልቁ ጉዳያቸው ነው ስትል ጋዜጠኛ ፍራንሴስካ ሮንችን ተናገረች፡፡
ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራት ቆይታ እንደገለጸችው፥ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊው ዶ/ር ቴወድሮስ ከጤና ጉዳዮች ይልቅ ለግል የፖለቲካ አቋማቸው ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጡ በተለያዩ ጊዜያት ከሚሰጧቸው መግለጫዎች መረዳት እንደሚቻል ግልፅ ማሳያዎች ናቸው ብላለች፡፡
ዶ/ር ቴወድሮስ መጋቢት 16 በጄኔቫ ተገኝተው በኮቪድ-19 እና በዩክሬን ቀውስ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በምድር ላይ ከትግራይ የበለጠ አደጋ ላይ ያሉ ሰዎች የሉም ማለታቸውና እሳቸውም የትግራይ ተወላጅ መሆናቸውን ደጋግመው ሲናገሩ መስማት አጅግ ያሳዝናል ብላለች፡፡
እንደ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የዩክሬን ሁኔታ ምላሽን የሚመለከቱ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ባሉበት ሁኔታ የግል ጉዳይ ማንሳት አግባብ አለመሆኑን የምትናገረው ጋዜጠኛዋ፥ መግለጫው በኢትዮጵያ ያሉ ሰብዓዊ ቀውሶችን ለማስታወስ ያለመ ከሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊው ሌሎች የተረሱ የአማራ እና የአፋር ክልል ሁኔታዎችንም ማንሳት ነበረባቸው ስትል ተችታለች፡፡
በአማራ እና በአፋር ክልል ያሉ ህዝቦች ከትግራይ ህዝብ ያነሰ ስጋት የለባቸውም ያለችው ፍራንሴስካ ሮንችን፥ በህወሀት እና በሸኔ ቡድን የአማራ ተወላጆች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ግድያ እየተፈፀመባቸው ነው ብላለች። ዶ/ር ቴወድሮስ ግን ስለዚህ ጉዳይ ለምን ትንፍሽ አላሉም ስትልም ጠይቃለች፡፡
በተጨማሪም ዶ/ር ቴወድሮስ በአማራ እና አፋር ክልል በህወሓት ቡድን በደረሰባቸው ውድመትና ዘረፋ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙና በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ ያለ አንዳች የህክምና አገልግሎት ሲንከራተት አንድም ቀን ተናግረው አያውቁም ስትልም ገልጻለች፡፡
“በእውነት ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሃላፊ ድርጊት በእጅጉ አሳዝኖኛል” ብላለች ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ ፍራንሴስካ ሮንችን ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር እንደመሆናቸው መጠን፥ በሌሎች ኢትዮጵያውያንምን ላይ የሚፈጸም እንዲህ ዓይነት ችግር ሊያሳስባቸው ይገባ ነበር ያለቸው ፍራንሴስካ፥ በቅርብ ጊዜ የወጣ ዘገባ እንደሚያመላክተው የአማራ እና አፋር ማህበረሰብ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን እና በርካታ የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ በመሆናቸው የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ውስንነቶች መኖራቸውን እንደምታውቅ ተናግራለች፡፡
በሁለቱ ክልሎች የተዘረፉና የወደሙ የጤና ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እየተወሰዱ ስላሉ የመለሶ ማቋቋም ስራዎች የዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊው ምንም ሳይናገሩ፥ በትግራይ ክልል ውስጥ አገልግሎት ስለማይሰጡ የጤና ተቋማት ብቻ ሲናገሩ ሲናገሩ በመስማቷ ቅሬታ እንደተሰማት ገልጻለች፡፡
የሚገርመው ግን ዶ/ር ቴወድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊነትን ሲረከቡ ያለአንዳች አድሎና ወገንተኝነት ለማገልገል የገቡትን ቃል ወደ ጎን በመተው የግል የፖለቲካ አቋማቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን የጠቆመችው ጋዜጠኛዋ፥ “የአድሎአዊነትን ገጽታ ለማመጣጠን እንኳ ምንም ግድ ያላቸው አይመስሉም” ብላለች።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በትዊተር፣ በፌስቡክ እና በሌሎች መድረኮች የሰጧቸው መግለጫዎች ሁሉ ህወሓት እና አጋሮቹን መሰረት ያደረጉ ናቸው ስትልም ነው ጋዜጠኛዋ የተናገረችው፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!