አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ባለፉት 6 ወራት ከምርት ሽያጭና አገልግሎት 271 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
የ2014 የ6 ወራት የስራ አፈጻጸምን አስመልክቶ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሃይለሚካኤል መግለጫ ሰጥቷል።
የግማሽ አመቱን የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ÷ የልማት ድርጅቶች በግማሽ አመቱ 263 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 271 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
ከጠቅላላ ገቢው በዘርፍ ደረጃ 56 በመቶው ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ፣ 23 ነጥብ 4 ቢሊየን ፋይናንስ እና 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ከኮሙኒኬሽን ዘርፍ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም ከእቅዱ በላይ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን÷ ውጤቱ የተመዘገበው ልማት ድርጅቶች የማምረት አቅማቸውና የአገልግሎት አሰጣጣቸው በማዘመናቸው የመጣ ውጤት ነው ተብሏል።
ድርጅቶቹ ከሀብት አባካኝነት ወደ ሀብት ፈጣሪነት መሸጋገራቸው አንዱ ለውጤቱ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው ብለዋል።
የልማት ድርጅቶች ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እያበረክቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነውም ነው ያሉት።
36 የልማት ድርጅቶች እንደሚገኙና 32ቱ ትርፋማ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን÷ አራቱ ኪሳራ ገጥሟቸዋል።
የልማት ድርጅቶቹ የውጭና የውስጥ የብድር እዳ አከፋፈል አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል አቶ ሀብታሙ።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በግማሽ አመቱ ለ12 ሺህ 260 ዜጐች የስራ እድል ፈጥሯልም ነው የተባለው፡፡
ለልማት ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የማምረቻ ግዥ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የሃይል አቅርቦት እጥረት፣ የፕሮጀክት አመራር ውስንነት በግማሽ አመቱ የተከሰቱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!