አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በከተማ ደረጃ በብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የመክረ የህዝብ የውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተገኝተዋል፡፡
ውይይቱ ብልፅግና ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተሰጠውን ሀገር የመምራትና የህዝብን ጥቅም የማረጋገጥ ከባድ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ ያስቀመጣቸው ወሳኝ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የህዝቡን ችግርና ሁለንተናዊ ፍላጎት በግልፅ ማንፀባረቅ ይችላሉ የተባሉ የህዝብ ተወካዮች እየሳተፉበት በሚገኘው በዚሁ ውይይት÷ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ አቅጣጫዎቹ ምን ያህል የህዝብን የቀደመ ፍላጎት ያገናዘበ ነው፣ የትኛቹ ጉዳዮችስ አሁንም ትኩረት ይሻሉ በሚሉ ሃሳቦች ላይ ተወያይቶ ለቀጣይ ስራ ወሳኝ ግብዓት ለማግኘት እንደሆነ አንስተዋል።
ብልፅግና በውይይት ያምናል ያሉት አቶ አደም÷ በለውጡ ዓመታት የተገኙ ስኬቶች እና የታዩ ችግሮች ላይ ውይይት ተደርጎ ለቀጣይ ከአቅጣጫዎቹ አፈፃፀም አንፃር ግብዓት ለማግኘት እውነተኛ መደማመጥና መተማመን ከህዝቡ ጋር እንዲፈጠር በጋራ ለመስራት በማመን ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ በበኩላቸው÷ ብልፅግና ለህዝብ ፍላጎት መሳካት የሚሰራ በመሆኑ የህዝቡን ሃሳብ ለማድመጥ የሰጠውን የውክልና ሃላፊነትም ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ነው ውይይቱ ያስፈለገው ብለዋል።
በስካይ ላይት እየተካሄደ ባለው በዚህ የህዝብ መድረክ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።
“በከተማዋ ውስጥ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግር፣ ጉዳይ በማስፈጸም ስም የሚንቀሳቀሱ ደላሎች ለህይወት ጭምር አደጋ መሆናቸውን፣ የሀላፊዎች መቀያየር ጉዳዮችን ለመፈጸም እንቅፋት ሆኗል ጉዳዮች በግለሰብ ሀላፊዎች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ” የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
“በአስተዳደሩ የተወሰኑ አሰራሮች በታችኛው ተቋማት በትክክል እየተተገበረ አይደለም፤ ብልጽግና ፓርቲ ጥላቻ ሰባኪዎችን ከመጠን በላይ ታግሷል፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች በተለይ ሴቶችና ህጻናት ትኩረት ይሰጣቸው፤ መሬትና ካርታ የዝቅተኛ አመራሮች አላግባብ መበልፀጊያ ሆነዋል” የሚሉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዋል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!