የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ድጋፉን በሚያጠናክርበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄደ

By Feven Bishaw

March 22, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ከዓለም ባንክ ቦርድ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ጋር ባንኩ ለኢትዮጵያ ድጋፉን በሚያጠናክርበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡

የዓለም ባንክ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ታውፊላ ንያማድዛቦ ከገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና ከጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ጋር ባንኩ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ ስለሚጠናከርበትና በባንኩ ድጋፍ እየተከናወኑ ባሉና ወደ ፊት በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ፍሪያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ስለተሰሩ ስራዎች፣ የልማት ድርጅቶችን ለማዘመንና ለማሻሻል ስለተደረጉ ጥረቶች፣ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት እንዲችሉ እየተሰጡ ስላሉ ድጋፎች፣ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች ውይይት ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ስለሚደረጉ ጥረቶች፣ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተሰጠ ስላለው ሰብዓዊ አርዳታ፣ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ የመገንባት ሂደት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስለመቋቋሙ ለባንኩ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ የልማት አጋር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለመሰረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ለሚሰጠው ድጋፍና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ያላቸውን ምስጋናም አቅርበዋል፡፡

ከዓለም አቀፉ የልማት ድርጅት የሚገኘው ሀብት የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የመጠጥ ውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በግጭት፣ በድርቅና በኮቪድ-19 ጉዳት ውስጥ አልፋ አሁንም በልማት ጎዳና ለመራመድ የምታደርገውን ጥረት መረዳታቸውን ጠቅሰው÷ የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የዓለም ባንክ በልማት አጋርነቱ እንደሚቀጥል ዶክተር ታውፊላ አረጋጠዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስት (ኢጋድ) እና ከአፍሪካ ህብረት ዋና ጸሐፊዎች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሸገር፣ የእንጦጦና የአንድነት ፓርኮችንም የጎበኙ ሲሆን÷ ከገንዘብ ሚኒስትሩና ከሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!