Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ እና ቻይና የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብሮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና በሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብሮች በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ማዕቀፍ ለቻይና ወገን በቀረቡት ነባርና አዲስ ፕሮጀክቶች ዙሪያም ሰፋ ያለ ምክክር ተደርጓል፡፡

በውይይቱ ወቅት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ኢትዮጵያ በርካታ መሰረተልማቶችን ለማጠናቀቅ የቻይና ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው በዳካር በተካሄደው የ8ኛው የቻይና አፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ በተቀመጡት ዘጠኝ ፕሮግራሞች መሰረት ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው አዳዲስ እና ነባር ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘውም እያደገ የመጣው የኢትዮጵያና የቻይና የኢኮኖሚ ልማት ትብብር የሁለቱ አገራት ግንኙነት የላቀ መሆኑን ማሳያ መሆኑን በመጠቆም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የጤናና የዲጂታል ኢኮኖሚ ትስስር የበለጠ በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትሰራለች ብለዋል፡፡

በቻይና የንግድ ሚኒስቴር የምዕራብ እስያና አፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ጂያንግ ሜይ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን በመጠቆም በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም የተቀመጡ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከኤምባሲው ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡

አያይዘውም የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ እንደሚያበረታቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version