አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአፋር ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በጦርነቱ ለተፈናቀሉ እና ዕድሜያቸው ከአንድ አመት በላይ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መስጠት የጀመሩት የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት÷ ከመጋቢት 12 እስከ 18 ለተከታታይ ሰባት ቀናት ይቆያል፡፡
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለዉ አባይነህ፥ ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልሎች እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች ላይ የቁጥጥር እና ምላሽ ስራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አራት ወረዳዎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ 674 ሰዎች የታመሙና ሰባት ሰዎች ደግሞ ለሞት በመዳረጋቸዉ÷ በወረዳዎቹ 98 በመቶ የመጀመሪያ ዙር የኮሌራ ክትባት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በአፋር ክልልም የኮሌራ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል ተብሎ በሚገመቱ የተመረጡና የተፈናቀሉ ዜጎች በሚገኙበት ስፈራ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በዞን 1፣ 2፣ 4 እና 5 በ16 ወረዳዎች በአጠቃላይ ለ174 ሺህ 780 ሰዎች እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ለዘመቻው አተገባበር ስኬትና የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚመለከታቸው አካላት የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
የአፋር ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ፈረጅ ሬብሳ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቁመው÷ በትንፋሽ የሚተላለፉ፣ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከሚደረጉ የመከላከል ሥራዎች አንዱ ክትባት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ የኮሌራ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር መሆኑን ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!