አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከኢድ እሰከ ኢድ ” በሚል ስያሜ ታላቁን ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በታላቁ የረመዳን ወር በኢትዮጵያ ታላቁ የኢድ ሶላት እንዲደረግ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ “ከኢድ እስከ ኢድ” በሚል ስያሜ ታላቁ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያን መረሀ ግብርን ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ የመርሀ ግብሩ አስፈፃሚ ብሔራዊ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን÷ የኮሚቴው አባላት በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርገዋል።
ኮሚቴውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና ኡስተዝ አቡበከር አህመድ በሰብሳቢነት መርተውታል።
በውይይቱ ላይ አምባሳደር ብርቱካን ባደረጉት ንግግር የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት አስመልክቶ በነበረው ታላቁ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸው÷ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በወሳኝ ወቅት ለሀገራቸው ያላቸውን ድጋፍ እና ፍቅር በተግባር ያሳዩበት እንደነበር አስታውሰዋል።
አምባሳደር ብርቱካን እንዳሉት፥ “ከኢድ እስከ ኢድ” በሚል ስያሜ የሚካሄደው ታላቁ የኢትዮጵያንውያን ጉዞ ኢትዮጵያ በሃይማኖት፣ በታሪክና በባህል ያሏትን እሴቶች ለዓለም የምታሳይበት መሆኑን ገልፀው፥ መርህ ግበሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
ለዝግጅቱ 16 መንግስታዊ ተቋማትን ያቀፈ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፥ ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በመሆን ነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት እና ሀላል ኘሮሞሽን የመርሀ ግብሩ አዘጋጆች መሆናቸው ተገልጿል።
የኮሚቴው ጣምራ ሊቀ መንበር ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እንዳሉት፥ በዓሉ ኢትዮጵያ ያላትን ቱባ እስላማዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ እና በጎ ተፅዕኖን በወዳጅ ሀገራት ዘንድ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ይሰናዳል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።