Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአማራ ክልል በጦርነት የደረሰበትን ችግር ለመሻገር ከክልሉ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን – የሩሲያ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጀኒ ተረኺን የአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት የደረሰበትን ውድመት ለመሻገር ከክልሉ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ኢቭጀኒ ተረኺን ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅትም አምባሳደር ኢቭጀኒ ተረኺን ከአማራ ክልል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በሰው ኀይል ልማት ዙሪያ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በዚህም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመሥራት ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ በከተማ ልማት ዙሪያ ከክልሉ ጋር እንደሚሠሩም አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በክልሉ አሸባሪው ቡድን ባደረሰው ዘርፈ ብዙ ጉዳት ምክንያት የደረሰውን ውድመት ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የሩሲያ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አያይዘውም ሩሲያና ኢትዮጵያ የቀደመ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በሚገጥማት ችግር ሁሉ ሩሲያ ከጎናችን ቆማ የምትደግፍ ሀገር ነች ለዚህም ምስጋና ይገባታል ብለዋል።
አሁንም በገባንበት የህልውና ጦርነት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ስብሰባዎችን ሲያካሂድ ሩሲያ ግን የኢትዮጵያን እውነት ተረድታ ከጎናችን በመቆም አብራን የታገለች አጋራችን ናት ሲሉም አክለዋል።
የአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት ያጋጠመውን ጉዳት በመልሶ ማቋቋም ተግባራት ሩሲያ እንድትደግፍም ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version