የሀገር ውስጥ ዜና

የድርቅ አደጋን ለመቋቋም ውሃን ማዕከል ያደረጉ ዘላቂ ሥራዎች ይሰራሉ – ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ

By Meseret Awoke

March 21, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድርቅ አደጋ በተከሰተ ቁጥር የዕለት ደራሽ እርዳታ በማቅረብ ብቻ መቋቋም ስለማይቻል ውሃን ማዕከል ያደረገ ዘላቂ ሥራዎች እንደሚሰሩ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ተናገሩ፡፡

የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ “ላኒና” ተብሎ በሚታወቀው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

በተለይም የአገሪቱ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተስብ ክፍሎች የዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

በዚህም ችግሩ ለደረሰባቸው 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ በፌደራል መንግሥት፣ በአጋር አካላትና በክልሎች ቅንጅት በመቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። የዕለት ደራሽ ድጋፉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን የያዘ መሆኑንም ገልጸው፥ አቅርቦቱ የሰውን ሕይወት ማዳን ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል።

በአርብቶ አደር አካባቢዎች የእንስሳት ኃብቱ ላይም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የእንስሳት መኖ በመቅረብ ላይ መሆኑንም አመላክተዋል።

ከዕለት ደራሽ እርዳታ አቅርቦቱ ባሻገርም ለሰውና ለእንስሳት የሚሆን ውኃ በቦቴዎች በመቅረብ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተጓዳኝም የውሃ ተቋማትን የመጠገን፣ የአስቸኳይ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ በርካታ የቁም እንስሳትን ለሞት በመዳረጉ በተለይም የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!