አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛ ዕዝ ከህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው ጀምሮ እስከ ኅብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ድረስ ከፍተኛ ተጋድሎ ላደረጉና ጀብድ ለፈፀሙ የሰራዊት ክፍሎች፣ አመራር እና አባላት የሜዳይና የማእረግ ማልበስ ስነ-ስርዓትአካሂዷል፡፡
የደቡብ እዝ ዋና አዛዥና የአድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚው ሌ/ጄ ሰለሞን ኢተፋ እንደገለጹት÷ 6ኛ ዕዝ ከሌሎች አጋር እዞች ጋር በመሆን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን አከርካሪ የሰበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የ6ኛ ዕዝ ዋና አዛዥና የላቀ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚው ሜ/ጄ ተስፋዬ ወልደኪዳን በበኩላቸው÷ 6ኛ ዕዝ የጥፋት ሃይሎች የሀገራችንን ህዝብ በመከፋፈል አገር የማፈራረስ እቅዳቸውን በህብረ ብሄራዊ ዘመቻ ቅዠት ሆኖ እንዲቀር በማድረግ የበኩሉን የጀግንነት ተግባር ፈጽሟል ብለዋል፡፡
የዕዙን የግዳጅ ውሎ ያቀረቡት መ/አ ሽመልስ ሹምየ÷ ዕዙ ከ47 በላይ የውጊያ ቀጠናዎች ላይ በመሳተፍ በሽብር ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን ገልፀው በአውደ ውጊያዎች ውሎም ድል በማስመዝገብ አገር ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
6ኛ እዝ 1ኛ ደረጃ የላቀ የአውደ ውጊያ ሜዳይ 31፣ 2ኛ ደረጃ የላቀ የአውደ ውጊያ ሜዳይ 50 እና 3ኛ ደረጃ የላቀ አውደ ውጊያ ሜዳይ 4 በድምሩ ለ85 ጀግኖች ሸልሟል።
በዕለቱ ለዕዙ በርካታ የሰራዊት አመራርና አባላት የማእረግ እድገትም የተሰጠ ሲሆን ዕዙ ባደረገው አገር የማዳን ተጋድሎ የተለያየ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም የምስክር ወረቀት መበርከቱን ከመከላከያ ሰራዊት የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!