Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለአገራዊ ራዕይ መሳካትና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአገራዊ ራዕይ መሳካትና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቀጣይ ለህዝብ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክትር ለገሰ ቱሉ÷ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ምክንያት በስሩ ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር በሚገባው ልክ ግንኙነት እንዳልነበረው አንስተዋል።
 
አሁን ተቋሙ ያዘጋጃቸውን መመሪያዎች እና አጠቃላይ አሰራሮችን በስሩ ከሚገኙ አካላት ጋር በመወያየት ለስኬታማነቱ የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
 
በተጨማሪም የኮሙኒኬሽን አካላት ከሚዲያ ተቋማት ጋር ይበልጥ ተቀራርበው በጋራ እንዲሰሩ ማስቻልም የመድረኩ ሌላኛው ዓላማ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ ብዝሃነት በተሻለ መልኩ እንዲጎለብት ተቋሙ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
 
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች÷ የመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን አካላት ግብ በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር በመሆኑ ተባብረው መስራት ግድ ይላል በማለት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ወደ ተግባር መሸጋገሩ ሚዲያዎች መረጃን በዘላቂነት እና ወጥ በሆነ መልኩ እንደያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም ነው የገለጹት።
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የደቡብ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁ በሰጡት አስተያየት÷ አንድ አገር እንዲያድግና እንዲቀየር ሚዲያና ኮሙኒኬሽን በእጅጉ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
 
ለአገር ብልጽግና መረጋገጥም “የህዝቦች አስተሳሰብ ሊለወጥ ግድ ነው” ያሉት ኃላፊዎቹ፥ ዜጎች የተሻለ እሳቤ ኖሯቸው ለአገር እንዲሰሩም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በውይይት መድረኩ ላይ የክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሮች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡
Exit mobile version