የሀገር ውስጥ ዜና

የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ በ10 ዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፍኖተ ካርታ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው – አቶ ንጉሡ ጥላሁን

By Meseret Awoke

March 19, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ በ10 ዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፍኖተ ካርታ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ፡፡

ከ200 ሺህ በላይ ምሩቃንን ያፈራው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዮት በ53ኛ ዙር 124 ተማሪዎቹን አስመርቋል።

ተማሪዎቹን የክብር እንግዳ ሆነው መመረቃቸውን ያበሰሩት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ፥ ለተመራቂዎቹ ማገልገል ጥበብ እና ትዕግስትን ይጠይቃል በማለት ኢትዮጵያ ያላትን ያልተነካ የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በኢትዮጵያ ከተቀመጡት ዋና ዋና 11 ዘርፎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ እና በ10ዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፍኖተ ካርታ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት እንዲያድግ እና አገርን እንዲጠቅም በዚህ ዓመት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ስር ሆኖ ከማዕከል ወደ ኢንስቲትዩት እንዲያድግ መደረጉን ገልፀዋል።

የቱሪዝም ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት፥ ተቋሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባደረገው ጥናት ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል የመመራት መጠኑ 33 በመቶ ብቻ በመሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት እና በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን በዚህ ዓመት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

ዛሬ በማታ እና መደበኛ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ያስመረቀው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት 53 ዓመታትን ያስቆጠረ እና 24 ቤተሙከራዎች ያሉት ተቋም መሆኑን ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!