የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል ግንባታቸው የተጓተቱና የተቋረጡ የልማት ፕሮጀክቶች አሰራር ዳግም እንዲፈተሸ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ

By Meseret Awoke

March 19, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ግንባታቸው የተጓተቱ እና የተቋረጡ የልማት ፕሮጀክቶች አሰራር ዳግም ሊፈተሸ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡

በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተትና መቋረጥ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ያነሱት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ፥ የክልሉ መንግስት የፕሮጀክቶችን አሰራር ዳግም ሊፈትሽ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት በጀመረው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔው ፥ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳ ያቀረቡትን የ2014 በጀት ዓመት የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል፡፡

በቀረበው ሪፖርት የክልሉ መንግስት ያስጀመራቸውና የህዝብን የልማት ችግር ይፈታሉ ተብለው በተለያዩ ቦታዎች የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጓተት የክልሉ ህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው ቀጥለዋል ነው ያሉት የምክር ቤት አባላቱ፡፡

የመንገድ፣ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመስኖ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በጅምር መቅረታቸውን የምክር ቤት አባላቱ ባደረግነው ምልከታ ታዝበናል ነው ያሉት፡፡

ከዚህም ባሻገር የክልሉ የስራ አጥ ዜጎችን ሁኔታ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በበጀት ዓመቱ ከለያቸው 506 ሺህ 217 ስራ አጥ ዜጎች ውስጥ 144 ሺህ 757 ዜጎች ብቻ የስራ እድል ማግኘታቸው አመርቂ ውጤት ባለመሆኑ አፅንዖት ሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባው መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሀብቶች በሚገባ ከተሰራባቸዉ የዜጎች የስራ አጥነት ችግር ሊፈቱ ስለሚችሉ ተለይተው ለዜጎች ጥቅም እንዲውሉ መሰራት አለበትም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ የተፈጥሮ ደን እየተጨፈጨፈ እንደሚገኝ እና ይህም አሳሳቢ እንደሆነ አባላቱ አንስተው ፥ በተለይ በጋሞ ዞን ከሰል ለማውጣትና ለማገዶ በሚል የተፈጥሮ ደን እየተጨፈጨፈ ስለሚገኝ ችግሩ ዕልባት ሊያገኝ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ ደኑን የምናጣበት ዕድል ሰፊ ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይም የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተው ፥ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪም ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አባላቱ አክለውም እንደሃገር እየታየ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር የክልሉን ህዝብ እንዳማረረ ገልጸው ፥ በመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ንረት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ነዉ የገለፁት፡፡

በምግብ አቅርቦቶች እና የፋብሪካ ውጤቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷልና የኑሮ ውድነቱን ማስታገስ በሚቻልበትና የህዝቡን ኑሮ ማረጋጋት በሚቻልበት ላይ የክልሉ መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

በተጨማሪም በደቡብና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ የህዝቡን ሰላም እያወከ እንደሚገኝም የምክር ቤት አባላቱ አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳ ከክልሉ ምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ዛሬ ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

በቢቂላ ቱፋ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!