አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዋና ዳይሬክተር ጋብሪኤላ ቡቸርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረግ አፋጣኝ ድጋፍን አስመልክተው መከሩ።
ድርቅ፣ ኮቪድ-19፣ ግጭት እና መፈናቀል በኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣሉን የጠቆሙት ሃላፊዎቹ ፥ ከኦክስፋም እና ከሌሎች የሰብዓዊ አጋሮች ሁለገብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ፥ በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን ኦክስፋምን ጨምሮ አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ለመደገፍ የኢትዮጵያ መንግስት ጥረት አድርጓል ።
ሶማሌ ክልል እና ቦረና እና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ 23 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ነው ያነሱት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አብራርተው ፥ ህወሓት በአጎራባች ክልሎች እየፈጸመ ያለው የሽብር ተግባር የመንግስትን ጥረት ማደናቀፉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ስላሉ አበረታች እርምጃዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ፥ ይህም መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ጠቅሰዋል።
አቶ ደመቀ ኦክስፋም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አድንቀው ፥ ድርጅቱ በሀገሪቱ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።
የኦክስፋም ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ፥ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ የሚደርሱ ችግሮች የበርካታ ሰዎች ህይወት ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ እንደሚገነዘብ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ የኦክስፋም ዳይሬክተር ፣ በአፍሪካ ቀንድ ፣ ምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ በኦክስፋም የቀጠናው የፕሮግራሞች ኃላፊ እና የአፍሪካ ህብረት የኦክስፋም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር አብረው መገኘታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!